፳፰
 ፩ በደኅና ከደረስን በኋላ በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንድትባል አወቅን።  ፪ አረማውያንም የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን።  ፫ ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው።  ፬ አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው። ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም አሉ።  ፭ እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት አንዳችም አልጐዳችውም፤  ፮ እነርሱም። ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው ብለው ይጠባበቁት ነበር ብዙ ጊዜ ግን ሲጠባበቁ በእርሱ ላይ የሚያስገርም ነገር ምንም ባላዩ ጊዜ። ይህስ አምላክ ነው ብለው አሳባቸውን ለወጡ።  ፯ በዚያም ስፍራ አጠገብ ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴት አለቃ መሬት ነበረ፥ እርሱም እንግድነት ተቀብሎን ሦስት ቀን በፍቅር አሳደረን።  ፰ የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው።  ፱ ይህም በሆነ ጊዜ የቀሩት ደግሞ በደሴቲቱ ደዌ የነበረባቸው እየመጡ ተፈወሱ፤  ፲ በብዙ ክብርም ደግሞ አከበሩን፥ በተነሣንም ጊዜ በመርከብ ላይ የሚያስፈልገንን ነገር አኖሩልን።  ፲፩ ከሦስት ወርም በኋላ በደሴቲቱ ከርሞ በነበረው በእስክንድርያው መርከብ ተነሣን፥ በእርሱም የዲዮስቆሮስ አላማ ነበረበት።  ፲፪ ወደ ሰራኩስም በገባን ጊዜ ሦስት ቀን ተቀመጥን፤  ፲፫ ከዚያም እየተዛወርን ወደ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ መጣን።  ፲፬ በዚያም ወንድሞችን አግኝተን በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ እንዲሁም ወደ ሮሜ መጣን።  ፲፭ ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ሰምተው እስከ አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ሊቀበሉን ወጡ፥ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ ልቡም ተጽናና።  ፲፮ ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት።  ፲፯ ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቆች ወደ እርሱ ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ሕዝቡን ወይም የአባቶችን ሥርዓት የሚቃወም አንዳች ሳላደርግ፥ ከኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ በሮማውያን እጅ አሳልፈው ሰጡኝ።  ፲፰ እነርሱም መርምረው ለሞት የሚገባ ምክንያት ስላልነበረብኝ ሊፈቱኝ አሰቡ፤  ፲፱ አይሁድ ግን በተቃወሙ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር ይግባኝ እንድል ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም።  ፳ ስለዚህም ምክንያት አያችሁና እነግራችሁ ዘንድ ጠራኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ ይህን ሰንሰለት ለብሻለሁና።  ፳፩ እነርሱም። እኛ ከይሁዳ ስለ አንተ ደብዳቤ አልተቀበልንም፥ ከወንድሞችም አንድ ስንኳ መጥቶ ስለ አንተ ክፉ ነገር አላወራልንም ወይም አልተናገረብህም።  ፳፪ ነገር ግን ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአልና የምታስበውን ከአንተ እንሰማ ዘንድ እንፈቅዳለን አሉት።  ፳፫ ቀንም ቀጥረውለት ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያው ወደ እርሱ መጡ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየመሰከረ ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ሕግና ከነቢያት ጠቅሶ እያስረዳቸው፥ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ይገልጥላቸው ነበር።  ፳፬ እኵሌቶቹም የተናገረውን አመኑ፥ እኵሌቶቹ ግን አላመኑም፤  ፳፭ እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ፥ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ሄዱ፤ እንዲህም አለ። መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ ለአባቶቻችን።  ፳፮ ወደዚህ ሕዝብ ሂድና። መስማትን ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትንም ታያላችሁና አትመለከቱም፤  ፳፯ በዓይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸው እንዳይሰሙ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል በላቸው  ፳፰ ሲል መልካም ተናገረ። እንግዲህ ይህ የእግዚአብሔር ደኅንነት ለአሕዛብ እንደ ተላከ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ እነርሱ ደግሞ ይሰሙታል።  ፳፱ ይህንም በተናገረ ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ።  ፴ ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፥ ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር፤  ፴፩ ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር።