የሐዋርያት ሥራ  
 ፩
 ፩-፫ ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው።  ፬ ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን። ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤  ፭ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ።  ፮ እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለው ጠየቁት።  ፯ እርሱም። አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤  ፰ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።  ፱ ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።  ፲ እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤  ፲፩ ደግሞም። የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።  ፲፪ በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።  ፲፫ በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም።  ፲፬ እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።  ፲፭ በዚህም ወራት ጴጥሮስ መቶ ሀያ በሚያህል በሰዎች ማኅበር አብረው በነበሩ በወንድሞቹ መካከል ተነሥቶ አለ።  ፲፮ ወንድሞች ሆይ፥ ኢየሱስን ለያዙት መሪ ስለሆናቸው ስለ ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ይገባ ነበር፤  ፲፯ ከእኛ ጋር ተቈጥሮ ነበርና፥ ለዚህም አገልግሎት ታድሎ ነበርና።  ፲፰ ይህም ሰው በዓመፅ ዋጋ መሬት ገዛ በግንባሩም ተደፍቶ ከመካከሉ ተሰነጠቀ አንጀቱም ሁሉ ተዘረገፈ፤  ፲፱ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ሁሉ ታወቀ፤ ስለዚህም ያ መሬት በቋንቋቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ፥ እርሱም የደም መሬት ማለት ነው።  ፳ በመዝሙር መጽሐፍ። መኖሪያው ምድረ በዳ ትሁን የሚኖርባትም አይኑር፤ ደግሞም። ሹመቱን ሌላ ይውሰዳት ተብሎ ተጽፎአልና።  ፳፩-፳፫ ኢዮስጦስም የሚሉትን በርስያን የተባለውን ዮሴፍንና ማትያስን ሁለቱን አቆሙ።  ፳፬-፳፮ ዕጣም ተጣጣሉላቸው፥ ዕጣውም ለማትያስ ወደቀና ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጠረ።