2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች  
 ፩
 ፩ በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ወንድሙም ጢሞቴዎስ፥ በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፤  ፪ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።  ፫ የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።  ፬ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፥ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን።  ፭ የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና።  ፮ ዳሩ ግን መከራ ብንቀበል፥ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ ብንጽናናም፥ እኛ ደግሞ የምንሣቀይበት በዚያ ሥቃይ በመጽናት ስለሚደረግ ስለ መጽናናታችሁ ነው።  ፯ ተስፋችንም ስለ እናንተ ጽኑ ነው፤ ሥቃያችንን እንደ ተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን ደግሞ እንድትካፈሉ እናውቃለንና።  ፰ በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤  ፱ አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር።  ፲-፲፪ ትምክህታችን ይህ ነውና፤ በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት በዚህ ዓለም ይልቁንም በእናንተ ዘንድ እንደኖርን የሕሊናችን ምስክርነት ነው።  ፲፫-፲፭ በዚህም ታምኜ፥ ሁለተኛ ጸጋ ታገኙ ዘንድ አስቀድሜ ወደ እናንተ እንድመጣ፥  ፲፮ በእናንተም መካከል ወደ መቄዶንያ እንዳልፍ ደግሞም ከመቄዶንያ ወደ እናንተ መጥቼ ወደ ይሁዳ በጉዞዬ እንድትረዱኝ አሰብሁ።  ፲፯ እንግዲህ ይህን ሳስብ ያን ጊዜ ቅሌትን አሳየሁን? ወይስ በእኔ ዘንድ አዎን አዎን አይደለም አይደለም ማለት እንዲሆን ያን የማስበው በዓለማዊ ልማድ ነውን?  ፲፰ እግዚአብሔር ግን የታመነ ነው፥ ለእናንተም የሚነገረው ቃላችን አዎንና አይደለም አይሆንም።  ፲፱ በእኛ ማለት በእኔና በስልዋኖስ በጢሞቴዎስም በመካከላችሁ የተሰበከ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አዎንና አይደለም አልነበረም፥ ነገር ግን በእርሱ አዎን ሆኖአል።  ፳ እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና፥ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ስለ ክብሩ በእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ ደግሞ ነው።  ፳፩ በክርስቶስም ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፥  ፳፪ ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው።  ፳፫ እኔ ግን ልራራላችሁ ስል እንደ ገና ወደ ቆሮንቶስ እንዳልመጣሁ በነፍሴ ላይ እግዚአብሔርን ምስክር እጠራለሁ።  ፳፬ ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ፥ በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም። በእምነታችሁ ቆማችኋልና።