፭
 ፩ እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤  ፪ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤  ፫ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤  ፬ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ።  ፭ እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።  ፮ እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤  ፯ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።  ፰ በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤  ፱ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።  ፲ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁምል ያበረታችሁማል።  ፲፩ ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።  ፲፪ እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ።  ፲፫ ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።  ፲፬ በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን። አሜን።