፳፩
 ፩ አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም።  ፪ ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ።  ፫ ታላቅም ድምፅ ከሰማይ። እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤  ፬ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።  ፭ በዙፋንም የተቀመጠው። እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም። እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ።  ፮ አለኝም። ተፈጽሞአል። አልፋና ዖሜጋ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ።  ፯ ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል።  ፰ ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው።  ፱ ሰባቱም ኋለኛዎች መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ። ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ።  ፲-፲፪ ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፥ አሥራ ሁለትም ደጆች ነበሩአት በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ፥ የአሥራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር።  ፲፫ በምሥራቅ ሦስት ደጆች፥ በሰሜንም ሦስት ደጆች፥ በደቡብም ሦስት ደጆች፥ በምዕራብም ሦስት ደጆች ነበሩ።  ፲፬ ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር።  ፲፭ የተናገረኝም ከተማይቱንና ደጆችዋን ቅጥርዋንም ይለካ ዘንድ የወርቅ ዘንግ ነበረው።  ፲፮ ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበራት፥ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋ ልክ ነበረ። ከተማይቱንም በዘንግ ለካት አሥራ ሁለትም ሺህ ምዕራፍ ሆነች፤ ርዝመትዋና ስፋትዋ ከፍታዋም ትክክል ነው።  ፲፯ ቅጥርዋንም ለካ፥ መቶ አርባ አራት ክንድ በሰው ልክ፥ እርሱም በመልአክ ልክ።  ፲፰ ቅጥርዋም ከኢያሰጲድ የተሠራ ነበረ፥ ከተማይቱም ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረች።  ፲፱ የከተማይቱም ቅጥር መሠረት በከበረ ድንጋይ ሁሉ ተጌጦ ነበር፤ ፊተኛው መሠረት ኢያሰጲድ፥ ሁለተኛው ሰንፔር፥ ሦስተኛው ኬልቄዶን፥ አራተኛው መረግድ፥  ፳ አምስተኛው ሰርዶንክስ፥ ስድስተኛው ሰርድዮን፥ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፥ ስምንተኛው ቢረሌ፥ ዘጠነኛው ወራውሬ፥ አሥረኛው ክርስጵራስስ፥ አሥራ አንደኛው ያክንት፥ አሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ።  ፳፩ አሥራ ሁለቱም ደጆች አሥራ ሁለት ዕንቆች ነበሩ፤ እየአንዳንዱ ደጅ ከአንድ ዕንቍ የተሠራ ነበረ። የከተማይቱም አደባባይ ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረ።  ፳፪ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም።  ፳፫ ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር።  ፳፬ አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፥ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፤  ፳፭ በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፥  ፳፮ የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርስዋ ያመጣሉ።  ፳፯ ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።