፰
 ፩ ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ።  ፪ ማለዳም ደግሞ ወደ መቅደስ ደረሰ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። ተቀምጦም ያስተምራቸው ነበር።  ፫ ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርሱዋን አቁመው።  ፬ መምህር ሆይ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች።  ፭ ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ? አሉት።  ፮ የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤  ፯ መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ። ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው።  ፰ ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ።  ፱ እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች።  ፲ ኢየሱስም ቀና ብሎ ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ። አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን? አላት።  ፲፩ እርስዋም። ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ አለች። ኢየሱስም። እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት።  ፲፪ ደግሞም ኢየሱስ። እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው።  ፲፫ ፈሪሳውያንም። አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም አሉት።  ፲፬ ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። እኔ ስለ ራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከወዴት እንደ መጣሁ ወዴትም እንድሄድ አታውቁም።  ፲፭ እናንተ ሥጋዊ ፍርድን ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በአንድ ሰው ስንኳ አልፈርድም።  ፲፮ የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁምና እኔ ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው።  ፲፯ የሁለት ሰዎችም ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአል።  ፲፰ ስለ ራሴ የምመሰክር እኔ ነኝ፥ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል።  ፲፱ እንግዲህ። አባትህ ወዴት ነው? አሉት። ኢየሱስ መልሶ። እኔንም ወይም አባቴንም አታውቁም፤ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር አላቸው።  ፳ ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር በግምጃ ቤት አጠገብ ይህን ነገር ተናገረ፤ ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም።  ፳፩ ኢየሱስም ደግሞ። እኔ እሄዳለሁ ትፈልጉኛላችሁም በኃጢአታችሁም ትሞታላችሁ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አላቸው።  ፳፪ አይሁድም። እኔ ወደ ምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም ማለቱ ራሱን ይገድላልን? እንጃ አሉ።  ፳፫ እናንተ ከታች ናችሁ፥ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፥ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም።  ፳፬ እንግዲህ። በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው።  ፳፭ እንግዲህ። አንተ ማን ነህ? አሉት። ኢየሱስም። ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት ነኝ።  ፳፮ ስለ እናንተ የምናገረው የምፈርደውም ብዙ ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ እውነተኛ ነው እኔም ከእርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ አላቸው።  ፳፯ ስለ አብ እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም።  ፳፰ ስለዚህም ኢየሱስ። የሰውን ልጅ ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ እኔ እሆን ዘንድ አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ።  ፳፱ የላከኝም ከእኔ ጋር ነው፤ እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና አብ ብቻዬን አይተወኝም አላቸው።  ፴ ይህን ሲናገር ብዙዎች በእርሱ አመኑ።  ፴፩ ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ። እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤  ፴፪ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው።  ፴፫ እነርሱም መልሰው። የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ። አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ? አሉት።  ፴፬ ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው።  ፴፭ ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘላለም ይኖራል።  ፴፮ እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ።  ፴፯ የአብርሃም ዘር መሆናችሁንስ አውቃለሁ ነገር ግን ቃሌ በእናንተ አይኖርምና ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ።  ፴፰ እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ደግሞ በአባታችሁ ዘንድ ያያችሁትን ታደርጋላችሁ።  ፴፱ መልሰውም። አባታችንስ አብርሃም ነው አሉት። ኢየሱስም። የአብሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር።  ፵ ነገር ግን አሁን ከእግዚእብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም።  ፵፩ እናንተ የአባታችሁን ሥራ ታደርጋላችሁ አላቸው። እኛስ ከዝሙት አልተወለድንም አንድ አባት አለን እርሱም እግዚአብሔር ነው አሉት።  ፵፪ ኢየሱስም አላቸው። እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና።  ፵፫ ንግግሬን የማታስተውሉ ስለ ምንድር ነው? ቃሌን ልትሰሙ ስለማትችሉ ነው።  ፵፬ እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።  ፵፭ እኔ ግን እውነትን የምናገር ስለ ሆንሁ አታምኑኝም።  ፵፮ ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው? እውነት የምናገር ከሆንሁ እናንተ ስለ ምን አታምኑኝም?  ፵፯ ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፤ እናንተ ከእግዚአብሔር አይደላችሁምና ስለዚህ አትሰሙም።  ፵፰ አይሁድ መልሰው። ሳምራዊ እንደ ሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ በማለታችን እኛ መልካም እንል የለምን? አሉት።  ፵፱ ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እኔስ ጋኔን የለብኝም ነገር ግን አባቴን አከብራለሁ እናንተም ታዋርዱኛላችሁ።  ፶ እኔ ግን የራሴን ክብር አልፈልግም፤ የሚፈልግ የሚፈርድም አለ።  ፶፩ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አያይም።  ፶፪ አይሁድ። ጋኔን እንዳለብህ አሁን አወቅን። አብርሃም ስንኳ ሞተ ነቢያትም፤ አንተም። ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አይቀምስም ትላለህ።  ፶፫ በእውኑ አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያትም ሞቱ፤ ራስህን ማንን ታደርጋለህ? አሉት።  ፶፬ ኢየሱስም መለሰ አለም። እኔ ራሴን ባከብር ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው፤  ፶፭ አላወቃችሁትምም፥ እኔ ግን አውቀዋለሁ። አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ሐሰተኛ በሆንሁ፤ ዳሩ ግን አውቀዋለሁ ቃሉንም እጠብቃለሁ።  ፶፮ አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው።  ፶፯ አይሁድም። ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት።  ፶፰ ኢየሱስም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው።  ፶፱ ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ።