፭
 ፩ ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።  ፪ በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት።  ፫ በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር።  ፬ አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር።  ፭ በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤  ፮ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ። ልትድን ትወዳለህን? አለው።  ፯ ድውዩም። ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።  ፰ ኢየሱስ። ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው።  ፱ ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ።  ፲ ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው። ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም አሉት።  ፲፩ እርሱ ግን። ያዳነኝ ያ ሰው። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ ብሎ መለሰላቸው።  ፲፪ እነርሱም። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን ነው? ብለው ጠየቁት።  ፲፫ ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ሰለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም።  ፲፬ ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና። እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው።  ፲፭ ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ።  ፲፮ ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር።  ፲፯ ኢየሱስ ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው።  ፲፰ እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር።  ፲፱ ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና።  ፳ አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል።  ፳፩ አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል።  ፳፪-፳፬ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።  ፳፭ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።  ፳፮ አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና።  ፳፯ የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው።  ፳፰-፴ እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።  ፴፩ እኔ ስለ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክሬ እውነት አይደለም፤  ፴፪ ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፥ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክር እውነት እንደ ሆነ አውቃለሁ።  ፴፫ እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችኋል እርሱም ለእውነት መስክሮአል።  ፴፬ እኔ ግን ከሰው ምስክር አልቀበልም፥ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ።  ፴፭ እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፥ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ።  ፴፮ እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና።  ፴፯ የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል። ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፥ መልኩንም አላያችሁም፤  ፴፰ እርሱም የላከውን እናንተ አታምኑምና በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም።  ፴፱ እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤  ፵ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።  ፵፩-፵፫ እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ።  ፵፬ እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?  ፵፭ እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው።  ፵፮ ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና።  ፵፯ መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?