፲፰
 ፩ ከዚህም በኋላ ጳውሎስ ከአቴና ወጥቶ ወደ ቆሮንቶስ መጣ።  ፪ በወገኑም የጳንጦስ ሰው የሚሆን አቂላ የሚሉትን አንድ አይሁዳዊ አገኘ፤ እርሱም ከጥቂት ጊዜ በፊት ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር ከኢጣልያ መጥቶ ነበር፥ አይሁድ ከሮሜ ይወጡ ዘንድ ቀላውዴዎስ አዞ ነበርና፤ ወደ እነርሱ ቀረበ፥  ፫ ሥራቸውም አንድ ስለ ነበረ በእነርሱ ዘንድ ተቀምጦ በአንድ ላይ ሠሩ፤ ሥራቸው ድንኳን መስፋት ነበረና።  ፬ በየሰንበቱም ሁሉ በምኵራብ ይነጋገር ነበር፥ አይሁድንና የግሪክንም ሰዎች ያስረዳ ነበር።  ፭ ሲላስና ጢሞቴዎስም ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ፥ ጳውሎስ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለአይሁድ እየመሰከረ ለቃሉ ይተጋ ነበር።  ፮ ነገር ግን በተቃወሙትና በተሳደቡ ጊዜ፥ ልብሱን እያራገፈ። ደማችሁ በራሳችሁ ነው፤ እኔ ንጹሕ ነኝ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ አላቸው።  ፯ ከዚያም ወጥቶ ኢዮስጦስ ወደሚባል እግዚአብሔርን ወደሚያመልክ ሰው ቤት ገባ ቤቱም በምኩራብ አጠገብ ነበረ።  ፰ የምኵራብ አለቃ ቀርስጶስም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ፥ ከቆሮንቶስ ሰዎችም ብዙ በሰሙ ጊዜ አምነው ተጠመቁ።  ፱-፲፩ በመካከላቸውም የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረ ዓመት ከስድስት ወር ተቀመጠ።  ፲፪ ጋልዮስም በአካይያ አገረ ገዥ በነበረ ጊዜ፥ አይሁድ በአንድ ልብ ሆነው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፥ ወደ ፍርድ ወንበርም አምጥተው።  ፲፫ ይህ ሕግን ተቃውሞ እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ ሰዎችን ያባብላል አሉ።  ፲፬ ጳውሎስም አፉን ሊከፍት ባሰበ ጊዜ፥ ጋልዮስ አይሁድን። አይሁድ ሆይ፥ ዓመፅ ወይም ክፉ በደል በሆነ እንድታገሣችሁ በተገባኝ፤  ፲፭ ስለ ቃልና ስለ ስሞች ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ ግን፥ ራሳችሁ ተጠንቀቁ እኔ በዚህ ነገር ፈራጅ እሆን ዘንድ አልፈቅድምና አላቸው።  ፲፮ ከፍርድ ወንበርም ፊት አስወጣቸው።  ፲፯ የግሪክ ሰዎችም ሁሉ የምኩራብ አለቃ ሶስቴንስን ይዘው በወንበሩ ፊት መቱት፤ በእነዚህም ነገሮች ጋልዮስ ግድ የለውም ነበር።  ፲፰ ከዚህም በኋላ ጳውሎስ እጅግ ቀን ተቀምጦ ወንድሞቹንም ተሰናብቶ በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ፤ ስለትም ነበረበትና ራሱን በክንክራኦስ ተላጨ፤ ጵርስቅላና አቂላም ከእርሱ ጋር ነበሩ።  ፲፱ ወደ ኤፌሶንም በደረሱ ጊዜ እነዚያን ከዚያ ተዋቸው፥ ራሱ ግን ወደ ምኵራብ ገብቶ ከአይሁድ ጋር ይነጋገር ነበር።  ፳ እነርሱም ብዙ ጊዜ እንዲቀመጥላቸው ሲለምኑት እሺ አላለም፤  ፳፩ ነገር ግን ሲሰናበታቸው። የሚመጣውን በዓል በኢየሩሳሌም አደርግ ዘንድ ይገባኛል እግዚአብሔር ቢፈቅድ ግን ወደ እናንተ ደግሞ እመለሳለሁ አላቸው። ከኤፌሶንም በመርከብ ተነሣ።  ፳፪ ወደ ቂሣርያም በደረሰ ጊዜ ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ።  ፳፫ ጥቂት ቀንም ቆይቶ ወጣ፥ ደቀ መዛሙርትንም ሁሉ እያጸና በገላትያ አገርና በፍርግያ በተራ አለፈ።  ፳፬ በወገኑም የእስክንድርያ ሰው የሆነ ነገር አዋቂ የነበረ አጵሎስ የሚሉት አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን ወረደ፤ እርሱም በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ።  ፳፭ እርሱ የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፥ የዮሐንስንም ጥምቀት ብቻ አውቆ በመንፈስ ሲቃጠል ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር ነበር።  ፳፮ እርሱም በምኵራብ ገልጦ ይናገር ጀመር። ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜ፥ ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት።  ፳፯ እርሱም ወደ አካይያ ማለፍ በፈቀደ ጊዜ፥ ወንድሞቹ አጸናኑት፥ ይቀበሉትም ዘንድ ወደ ደቀ መዛሙርት ጻፉለት፤ በደረሰም ጊዜ አምነው የነበሩትን በጸጋ እጅግ ይጠቅማቸው ነበር፤  ፳፰ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ከመጻሕፍት እየገለጠ ለአይሁድ በሁሉ ፊት በጽኑ ያስረዳቸው ነበርና።