፲፮
 ፩ ወደ ደርቤንና ወደ ልስጥራንም ደረሰ። እነሆም፥ በዚያ የአንዲት ያመነች አይሁዳዊት ልጅ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ አባቱ ግን የግሪክ ሰው ነበረ።  ፪ ለእርሱም በልስጥራንና በኢቆንዮን ያሉ ወንድሞች መሰከሩለት።  ፫ ጳውሎስ ይህ ከእርሱ ጋር ይወጣ ዘንድ ወደደ፥ በእነዚያም ስፍራዎች ስለ ነበሩ አይሁድ ይዞ ገረዘው፤ አባቱ የግሪክ ሰው እንደ ሆነ ሁሉ ያውቁ ነበርና።  ፬ በከተማዎችም ሲዞሩ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የቈረጡትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ሰጡአቸው።  ፭ አብያተ ክርስቲያናትም በሃያማኖት ይበረቱ ነበር፥ በቍጥርም ዕለት ዕለት ይበዙ ነበር።  ፮ በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ፤  ፯ በሚስያም አንጻር በደረሱ ጊዜ ወደ ቢታንያ ይሄዱ ዘድን ሞከሩ፥ የኢየሱስ መንፈስም አልፈቀደላቸውም፤  ፰ በሚስያም አጠገብ አልፈው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ።  ፱ ራእይም ለጳውሎስ በሌሊት ታየው፤ አንድ የመቄዶንያ ሰው። ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን እያለ ቆሞ ሲለምነው ነበር።  ፲ ራእዩንም ካየ በኋላ ወዲያው ወደ መቄዶንያ ልንወጣ ፈለግን፥ ወንጌልን እንሰብክላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ጠራን መስሎናልና።  ፲፩ ከጢሮአዳም ተነሥተን በቀጥታ ወደ ሳሞትራቄ በነገውም ወደ ናጱሌ በመርከብ ሄድን፤  ፲፪ ከዚያም ወደ ፊልጵስዩስ ደረስን፤ እርስዋም የመቄዶንያ ከተማ ሆና የወረዳ ዋና ከተማና ቅኝ አገር ናት፤ በዚህችም ከተማ አንዳንድ ቀን እንቀመጥ ነበር።  ፲፫ በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን።  ፲፬ ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።  ፲፭ እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ። በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን።  ፲፮ ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን።  ፲፯ እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች። የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር።  ፲፰ ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን። ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።  ፲፱ ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤  ፳ ወደ ገዢዎችም አቅርበው። እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ።  ፳፩ እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ አሉ።  ፳፪ ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፥ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤  ፳፫ በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት።  ፳፬ እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፥ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው።  ፳፭ በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር  ፳፮ ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ የሁሉም እስራት ተፈታ።  ፳፯ የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ።  ፳፰ ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ። ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ ብሎ ጮኸ።  ፳፱ መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፥ እየተንቀጠቀጠም ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ፤  ፴ ወደ ውጭም አውጥቶ። ጌቶች ሆይ፥ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል? ኣላቸው።  ፴፩ እነርሱም። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ አሉት።  ፴፪ ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሩአቸው።  ፴፫ በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፥ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ፤  ፴፬ ወደ ቤቱም አውጥቶ ማዕድ አቀረበላቸው፥ በእግዚአብሔርም ስላመነ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሤት አደረገ።  ፴፭ በነጋም ጊዜ ገዢዎቹ። እነዚያን ሰዎች ፍታቸው ብለው ሎሌዎቻቸውን ላኩ።  ፴፮ የወኅኒውም ጠባቂ። ትፈቱ ዘንድ ገዢዎቹ ልከዋል፤ እንግዲህ አሁን ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ ብሎ ይህን ቃል ለጳውሎስ ነገረው።  ፴፯ ጳውሎስ ግን። እኛ የሮሜ ሰዎች ስንሆን ያለ ፍርድ በሕዝብ ፊት ደብድበው በወኅኒ ጣሉን፤ አሁንም በስውር ይጥሉናልን? አይሆንም ራሳቸው ግን መጥተው ያውጡን አላቸው።  ፴፰ ሎሌዎቹም ይህን ነገር ለገዢዎች ነገሩ። የሮሜ ሰዎችም እንደ ሆኑ በሰሙ ጊዜ ፈሩ፤  ፴፱ መጥተውም ማለዱአቸው፥ አውጥተውም ከከተማ ይወጡ ዘንድ ለመኑአቸው።  ፵ ከወኅኒውም ወጥተው ወደ ልድያ ቤት ገቡ፥ ወንድሞችንም ባዩ ጊዜ አጽናኑአቸውና ሄዱ።