፲፫
 ፩ ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።  ፪ እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካገባ በኋላ፥  ፫ ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥  ፬ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤  ፭ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ።  ፮ ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን? አለው።  ፯ ኢየሱስም መልሶ። እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፥ በኋላ ግን ታስተውለዋለህ አለው።  ፰ ጴጥሮስም። የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም አለው። ኢየሱስም። ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ብሎ መለሰለት።  ፱ ስምዖን ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም አለው።  ፲ ኢየሱስም። የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፥ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም አለው።  ፲፩ አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና፤ ስለዚህ። ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም አለው።  ፲፪ እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው። ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?  ፲፫ እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ።  ፲፬ እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል።  ፲፭ እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና።  ፲፮ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም።  ፲፯ ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ።  ፲፰ ስለ ሁላችሁ አልናገርም፤ እኔ የመረጥኋቸውን አውቃለሁ፤ ነገር ግን መጽሐፍ። እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው።  ፲፱ በሆነ ጊዜ እኔ እንደ ሆንሁ ታምኑ ዘንድ፥ ከአሁን ጀምሬ አስቀድሞ ሳይሆን እነግራችኋለሁ።  ፳ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ማናቸውን የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።  ፳፩ ኢየሱስ ይህን ብሎ በመንፈሱ ታወከ መስክሮም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል አለ።  ፳፪ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ማን እንደ ተናገረ አመንትተው እርስ በርሳቸው ተያዩ።  ፳፫ ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ፤  ፳፬ ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ እርሱን ጠቅሶ። ስለማን እንደ ተናገረ ንገረን አለው።  ፳፭ እርሱም በኢየሱስ ደረት እንዲህ ተጠግቶ። ጌታ ሆይ፥ ማን ነው? አለው።  ፳፮ ኢየሱስም። እኔ ቍራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው ብሎ መለሰለት። ቍራሽም አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ለስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው።  ፳፯ ቍራሽም ከተቀበለ በኋላ ያን ጊዜ ሰይጣን ገባበት። እንግዲህ ኢየሱስ። የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ አለው።  ፳፰ ነገር ግን ከተቀመጡት ስለ ምን ይህን እንዳለው ማንም አላወቀም፤  ፳፱ ይሁዳ ከረጢቱን የያዘ ስለ ሆነ፥ ኢየሱስ። ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ፥ ወይም ለድሆች ምጽዋት እንዲሰጥ ያለው ለአንዳንዱ መስሎአቸው ነበርና።  ፴ እርሱም ቍራሹን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው ወጣ፤ ሌሊትም ነበረ።  ፴፩ ከወጣም በኋላ ኢየሱስ እንዲ አለ። አሁን የሰው ልጅ ከበረ እግዚአብሔርም ሰለ እርሱ ከበረ፤  ፴፪ እግዚአብሔር ስለ እርሱ የከበረ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን ራሱን ያከብረዋል ወዲያውም ያከብረዋል።  ፴፫ ልጆች ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድም። እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፥ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ።  ፴፬ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።  ፴፭ እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።  ፴፮ ስምዖን ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ ወዴት ትሄዳለህ? አለው። ኢየሱስም። ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፥ ነገር ግን በኋላ ትከተለኛለህ ብሎ መለሰለት።  ፴፯ ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ አሁን ልከተልህ አለመቻሌ ስለ ምንድር ነው? ነፍሴን ስንኳ ስለ አንተ እሰጣለሁ አለው።  ፴፰ ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰለት። ነፍስህን ስለ እኔ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዶሮ አይጮኽም።