፭
 ፩ ሐናንያም የተባለ አንድ ሰው ሰጲራ ከተባለች ከሚስቱ ጋር መሬት ሸጠ፥  ፪ ሚስቱም ደግሞ ስታውቅ ከሽያጩ አስቀረና እኩሌታውን አምጥቶ በሐዋርያት እግር አጠገብ አኖረው።  ፫ ጴጥሮስም። ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለ ምን ሞላ?  ፬ ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህን ነገር ስለ ምን በልብህ አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው።  ፭ ሐናንያም ይህን ቃል ሰምቶ ወደቀ ሞተም፤ በሰሙትም ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ።  ፮ ጐበዞችም ተነሥተው ከፈኑት አውጥተውም ቀበሩት።  ፯ ከሦስት ሰዓት ያህል በኋላም ሚስቱ የሆነውን ሳታውቅ ገባች።  ፰ ጴጥሮስም መልሶ። እስቲ ንገሪኝ፥ መሬታችሁን ይህን ለሚያህል ሸጣችሁትን? አላት። እርስዋም። አዎን፥ ይህን ለሚያህል ነው አለች።  ፱ ጴጥሮስም። የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ ስለ ምን ተስማማችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር በደጅ ነው አንቺንም ያወጡሻል አላት።  ፲ ያን ጊዜም በእግሩ አጠገብ ወደቀች ሞተችም፤ ጐበዞችም ሲገቡ ሞታ አገኙአት አውጥተውም በባልዋ አጠገብ ቀበሩአት።  ፲፩ በቤተ ክርስቲያን ሁሉና ይህንም በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ።  ፲፪ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ነበሩ።  ፲፫ ከሌሎችም አንድ ስንኳ ሊተባበራቸው የሚደፍር አልነበረም፥  ፲፬ ሕዝቡ ግን ያከብሩአቸው ነበር፤ የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ።  ፲፭ ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር።  ፲፮ ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለችው ከተማ ድውያንንና በርኵሳን መናፍስት የተሣቀዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበስቡ ነበር፤ ሁሉም ይፈወሱ ነበር።  ፲፯ ሊቀ ካህናቱ ግን የሰዱቃውያን ወገን ሆነውም ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ተነሡ ቅንዓትም ሞላባቸው።  ፲፰ በሐዋርያትም ላይ እጃቸውን ጭነው በሕዝቡ ወኅኒ ውስጥ አኖሩአቸው።  ፲፱ የጌታ መልአክ ግን በሌሊት የወኅኒውን ደጅ ከፍቶ አወጣቸውና።  ፳ ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ አላቸው።  ፳፩ በሰሙም ጊዜ ማልደው ወደ መቅደስ ገብተው አስተማሩ። ግን ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው ሸንጎውንና የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድነት ጠሩ፥ ያመጡአቸውም ዘንድ ወደ ወኅኒ ላኩ።  ፳፪-፳፬ የመቅደስ አዛዥና የካህናት አለቆችም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ። እንጃ ይህ ምን ይሆን? እያሉ ስለ እነርሱ አመነቱ።  ፳፭ አንድ ሰውም መጥቶ። እነሆ፥ በወኅኒ ያኖራችኋቸው ሰዎች እየቆሙ ሕዝቡንም እያስተማሩ በመቅደስ ናቸው ብሎ አወራላቸው።  ፳፮ በዚያን ጊዜ አዛዡ ከሎሌዎች ጋር ሄዶ አመጣቸው፥ በኃይል ግን አይደለም፤ ሕዝቡ እንዳይወግሩአቸው ይፈሩ ነበርና።  ፳፯ አምጥተውም በሸንጎ አቆሙአቸው።  ፳፰ ሊቀ ካህናቱም። በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው።  ፳፱ ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ። ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል።  ፴ እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው፤  ፴፩ ይህን እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ፥ ራስም መድኃኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው።  ፴፪ እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፥ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።  ፴፫ እነርሱም ሲሰሙ በጣም ተቈጡ ሊገድሉአቸውም አሰቡ።  ፴፬ ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፥  ፴፭ እንዲህም አላቸው። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።  ፴፮ ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ። እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፥ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ እንደ ምናምንም ሆኑ።  ፴፯ ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ።  ፴፰ አሁንም እላችኋለሁ። ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤  ፴፱ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።  ፵ ሰሙትም፥ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው።  ፵፩ እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤  ፵፪ ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።