1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች  
 ፩
 ፩ ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር አብ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን።  ፪-፬ በእግዚአብሔር የምትወደዱ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ተመረጣችሁ አውቀናልና።  ፭ ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ።  ፮ ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፥ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤  ፯ ስለዚህም በመቄዶንያና በአካይያ ላሉት ምእመናን ሁሉ ምሳሌ ሆናችሁላቸው።  ፰-፲ ከእናንተ ወጥቶ የጌታ ቃል በመቄዶንያና በአካይያ ብቻ አልተሰማምና፥ ነገር ግን ምንም እንድንናገር እስከማያስፈልግ ድረስ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚሆን እምነታችሁ በሁሉ ስፍራ ተወርቶአል።